- በዕርቀ ሰላም ሒደቱና መግለጫው ስለ በጋሻው ደሳለኝ የተጠቀሰ ነገር የለም
- የምእመናን ተወካዮች በጋሻው ይቅርታ እንዲጠይቅ የተሰጠውን ፈቃድ ተቃውመዋል
- በጋሻው ደሳለኝ ይቅርታ የመጠየቁን ፈቃድ እንዲያገኝ በፓትርያርኩና በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ ላይ የክልል እና ፌዴራል ግለሰብ ባለሥልጣናት ጫና መደረጉ ተጠቁሟል
የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሲዳማና ጉጂ ቦረና አህጉረ ስብከት ልኡክ ዛሬ፣ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የዕርቀ ሰላም ስምምነት መግለጫ በሚያወጣበት በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ገዳም በጋሻው ደሳለኝ ‹‹ሕዝቡን ይቅርታ ለመጠየቅ›› ፈቃድ ማግኘቱ ተሰማ፡፡
በጋሻው ደሳለኝ ይቅርታ የመጠየቅ ፈቃድ ማግኘቱ የታወቀው÷ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የዕርቀ ሰላም ልኡኩ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ትላንት፣ ከቀትር በኋላ ወደ ሐዋሳ ደ/ምሕ/ቅ/ገብርኤል ገዳም ምእመናን ተወካዮች ስልክ በመደወል፣ በመግለጫው ላይ በጋሻው ምእመኑን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበትና እንደተፈቀደለት፣ የምእመናን ተወካዮቹ በዚህ እንዲስማሙና የማይስማሙ ከኾነ እርሳቸውም እንደማይገኙ ባስታወቁ ጊዜ ነው፡፡
ዋነኛው የዕርቀ ሰላም ንግግር በተደረገበት ኅዳር ፭ እና ፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም በተያዘው ቃለ ጉባኤና በተዘጋጀው መግለጫ ላይ የበጋሻው ስም እንኳ እንዳልተነሣ የሚጠቅሱት የምእመናን ተወካዮች፣ የዕርቀ ሰላም ስምምነቱ የሐዋሳ ችግር ብቻ የተዘረዘረበትና የከተማውን ምእመናን ብቻ የሚመለከት እንደኾነ ለብፁዕ ዋና ጸሐፊው ለማስረዳት ቢሞክሩም ብፁዕነታቸው በአቋማቸው በመጽናታቸው ተቀባይነት እንዳላገኙ ተገልጦአል፡፡
የምእመናን ተወካዮቹ ተቃውሞ፣ ግለሰቡ በዕርቀ ሰላም ስምምነት ውስጥ አለመጠቀሱ ብቻ ሳይኾን የሐዋሳ ከተማ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ነዋሪ ምእመን አለመኾኑና ኦርቶዶክሳዊ ትምህርተ ሃይማኖትንና ክርስቲያናዊ ትውፊትን በመፃረር በተናገራቸውና በጻፋቸው ሕጸጾች የበደለው የሐዋሳን ብቻ ሳይኾን ቤተ ክርስቲያንንና በርካታ ኦርቶዶክሳውያን መኾኑን፣ ስለዚህም ከፍተኛ በደሉ በታኅሣሥ ወር ፳፻፬ ዓ.ም. በተቋቋመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ጉባኤ ጉዳዩ የተያዘ መኾኑን የሚጠቅስ ጭምር ነው፡፡
በዛሬው የዕርቀ ሰላም መግለጫ በጋሻው የተፈቀደለት የአቋራጭ ይቅርታ ዕድል ተቀባይነት እንደሌለውና ግለሰቡ እንደለመደው ለጥያቄ የሚፈለግበትን ጉዳይ ለማዘናጋትና ለመሸፈን ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የምእመናኑ ተወካዮቹ ይገልጻሉ፡፡ የበጋሻው ጉዳይ በሒያጅና በአማላጅ የማይፈታ ሃይማኖታዊ ከመኾኑም አንጻር በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንና የግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. ቅ/ሲኖዶስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ‹‹ለጥያቄ ቀርቦና ጉዳዩ ተጣርቶ እንዲቀርብ›› ሲል በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ቀኖናዊ አካሄዱን ጠብቆ እንዲታይ በጥብቅ አሳስበዋል፡፡
ብፁዕ ዋና ጸሐፊው የበጋሻው ጉዳይ ሃይማኖታዊ መኾኑንና በተያዘው መንገድ ማለቅ እንዳለበት ከዕርቀ ሰላሙ ሒደት መጀመሪያ አንሥቶ ደጋግመው ሲናገሩ እንደነበር ያስታወሱ የዜናው ምንጮች፣ አኹን በድንገት የተሰማው የአቋም ለውጥ በሒደቱ ምልክቱን ሲታዘቡት የቆዩት ውጫዊ ተጽዕኖ ጉልሕ ማሳያ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የሐዋሳ ጉዳይ በዕርቅ ማለቅ እንዳለበት ከመንግሥት በተጠቆመው መሠረት››የሚሉ አገላለጾች በዕርቀ ሰላም መግለጫው ውስጥ መታዘባቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
ይህም ኾኖ ጉዳዩን በዕርቅ ለመጨረስ ሁለቱም ወገኖች በተስማሙበት መሠረት ለኅዳር ወር መጨረሻ ቀጠሮ ከተያዘና ቀጠሮውና ጅምሩ የቋሚ ሲኖዶሱን ይኹንታ አግኝቶ ሳለ፣ በጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ በአጀንዳነት ካልተያዘ በሚል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተደጋጋሚ መወትወታቸው በምልአተ ጉባኤው አባላት ዘንድ በበጎ አልታየም፡፡
የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች እንደሚሉት÷ ‹‹ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ይነሡ፣ የሐዋሳ ደ/ምሕ/ቅ/ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ፣ ሰንበት ት/ቤትና ልማት ኮሚቴ ፈርሶ እንደ አዲስ ይቋቋም›› በማለት የሚጠይቁ 30 ግለሰቦች በስብሰባው ሰሞን ከሐዋሳ፣ ክብረ መንግሥትና ነገሌ ቦረና ከተሞች ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ከትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋራ መገናኘታቸውን ተከትሎ ሚኒስትሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን በቢሯቸው ማነጋገራቸው ተገልጦአል፡፡ ግለሰቦቹም በፓትርያርኩ አመልካችነት የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ወደ ደቡብ ኮርያ – ሴዑል በሄዱበት አጋጣሚ በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ይህም ሁሉ ኾኖ ምልአተ ጉባኤው ጉዳዩ በአጀንዳ ተይዞ እንወስንበት የሚለውን ሐሳብ በከፍተኛ ድምፅ ውድቅ በማድረግ፣ ‹‹ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ለያዙት የዕርቀ ሰላም ጥረት ሌሎችን ጨምረን የዕርቀ ሰላም ስምምነቱን ያወርዱ›› በሚል ሁለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በተጨማሪነት ሠይሟል፤ ስምምነቱንና ዕርቀ ሰላሙን አስፈጽመው የመጨረሻ የዕርቁን ሰነድም ለምልአተ ጉባኤው እንዲያቀርቡ ብቻ ነበር ውሳኔው፡፡
ለበጋሻው የተሰጠው በአቋራጭ ይቅርታ የመጠየቅ ፈቃድ በአንድ በኩል ወትሮም ሒደቱን ይተቹ የነበሩ ወገኖች የሚያነሡትን ጥርጣሬ የሚያጠናክር እንደኾነ አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡ በሌላም በኩል ከዕርቀ ሰላሙ በኋላ በሚኖሩ የስምምነቱ አፈጻጸሞችና አገልግሎት ላይም ሊኖረን የሚገባውን ንቁና ያልተቋረጠ ክትትል በእጅጉ አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment