Thursday, November 7, 2013

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በአሜሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ትላንት አሜሪካን መዲና ዋሺንግተን ዲሲ ገብተዋል

His Holiness Abune Mathias
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (ፎቶ: ማኅበረ ቅዱሳን)
  • ለ10 ዓመታት (ከ፲፱፻፸፬ – ፲፱፹፬ ዓ.ም.) በስደት፣ ለ15 ዓመታት (፲፱፹፬- ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.)  በሐዋርያዊ አገልግሎት ቆይተውበታል፡፡
  • በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ በኒውዮርክ ከተመሠረተውና የጃማይካ ተወላጆች ከሚገኙበት የኒውዮርክ ቅድስ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ቀጥሎ የመጀመሪያውን የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በዋሽንግተን ዲሲ (መካነ ሕይወት መድኃኔዓለም) አቋቁመዋል፡፡
  • ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያን መዋቅርንና የሁለተኛ ሲኖዶስ  ምሥረታን በመቃወም የእናት ቤተ ክርስቲያን እንቅሰቃሴመርተዋል፡፡


  • የትኛውም አካል ባላሰበበት ዘመን ስለ ዕርቀ ሰላም አሳስበዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንና ሌሎች በስደት የሚገኙ አባቶችን በአትላንታ ጆርጅያ በአካል አግኝተው ከተወያዩ በኋላ ለኢትዮጵያው ቅ/ሲኖዶስ መልእክት በመላክ ዕርቀ ሰላም እንዲጀመር መሠረት ጥለዋል፡፡
  • ቃለ ዐዋዲው ለሰሜን አሜሪካ ሀ/ስብከት እንዲስማማ ኾኖ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው በቅዱስነታቸው የሰሜን አሜሪካ ቆይታ ዘመን ነው፡፡
  • ‹‹ተዐቀቡኬ እምሐሳውያን ነብያት›› በሚል ርእስ በዋሽንግተን ዲሲ በተዘጋጀው ከፍተኛ ጉባኤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሤራ ቤተ ክርስቲያንን እያወካት መኾኑን በመግለጽ ካህናትና ምእመናን በብርቱ እንዲቋቋሙት አጠንክረው አስተምረዋል፤ በእመቤታችን ቅድስና ላይ የስሕተት ትምህርት ለማስተማር የሞከሩ ካህናትን በመምከር ከስሕተታቸው አልመለስ ያሉትን አውግዘው በመለየት ሃይማኖታዊ ቅንዐታቸውን በተግባር ገልጸዋል፡፡
  • ‹‹የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን መረከብ አንፈልግም፤ ታሪካዊ አንድነታችንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያናችን መጠበቅ አለበት›› በሚል የተነሣሣውን የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች እንቅሰቃሴ በማጠናከር የሰንበት ት/ቤቶች እንዲስፋፉ አድርገዋል፡፡ በሀ/ስብከቱ ማኅበረ ቅዱሳን በእናት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር የሚያበረክተው አገልግሎት እንዲጠናከር የማይቋርጥ ምክርና አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
  • ቅዱስነታቸው በአሜሪካ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከሢመተ ፕትርክናቸው ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚያካሂዱት ነው፡፡
  • ‹‹የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት የቤተ ክርስቲያናችንን ልዕልና የሚያሳይ ለካህናትና ለምእመናን መንፈሳዊ ኩራት ስለኾነ በቂ የቅድሚያ ዝግጅት እየተደረገ በውጭ ሀገርም ሳይቀር ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡›› /ከመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ፴፪ው ዓመታዊ ስብሰባ የአቋም መግለጫ/
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከነገ ጥቅምት ፳፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ ለዐሥር ቀናት የሚቆይ ሐዋርያዊ ጉብኝት በአሜሪካ ለማድረግ ዛሬ ማምሻውን ይጓዛሉ፡፡
ቅዱስነታቸው ሢመተ ፕትርክናቸው ከተፈጸመበት የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ወዲህ የመጀመሪያቸው በኾነው በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውየዋሽንግተን ዲሲ ሜሪላንድ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን የምረቃ ሥነ ሥርዐት እንደሚያከናውኑ ከልዩ ጽ/ቤታቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ የቋሚ ቅ/ሲኖዶስ አባላት የኾኑት÷ የደቡብ ትግራይ እና ማይጨው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዴዎስቆሮስ እንዲሁም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አብረዋቸው እንደሚጓዙ ተገልጧል፡፡
በቅርቡ ፴፪ውን ዓመታዊ ስብሰባውን ያካሄደውና በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት የተካተተውን የውጭ ግንኙነት መምሪያ ዘገባ ያዳመጠው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ በአቋም መግለጫው ተ.ቁ(3)÷ ቅዱስነታቸው በአገር ውስጥ ይኹን በውጭ የሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያናችንን ልዕልና የሚያሳዩ፣ ለካህናትና ለምእመናን መንፈሳዊ ኩራት›› ናቸው፡፡ በመኾኑም ‹‹የቅድሚያ ዝግጅት እየተደረገ በውጭ ሀገርም ሳይቀር ተጠናክሮ እንዲቀጥል›› አጠቃላይ ጉባኤው ድጋፉን ሰጥቷል፡፡
በሢመተ ፕትርክናቸው ወቅት የወጡ ኅትመቶች እንደሚያስረዱት፣ ቅዱስነታቸው በአሜሪካ በስደት በቆዩባቸው ዐሥር ዓመታትና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በመኾን ባገለገሉባቸው ዐሥራ አምስት ዓመታት በኻያ ያህል ግዛቶች በአጠቃላይ ኻያ አምስት አብያተ ክርስቲያንን አቋቁመዋል፡፡ እኒህም ዛሬ በሦስት አህጉረ ስብከት ተከፍሎ በሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ለሚመራው የአህጉረ ስብከቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ‹‹እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መንገድ ጠራጊ ፋና ወጊ ኾነውለታል፡፡›› – ‹‹ዛሬ በሦስት አህጉረ ስብከት ተከፋፍሎ የሚታየው የሰሜን አሜሪካ አገልግሎት ብቻቸውን በመኾን ምግብ አብስሎ የሚያቀርብላቸው በሌለበት ራሳቸው ቄስ፣ ራሳቸው ዲያቆን አንዳንዴም ሹፌር በመኾን ከዳር እስከ ዳር አገልግለውበታል፡፡››
በሰሜን አሜሪካ ጎልቶ የሚታየውን የገለልተኝነት መዋቅርና አስተዳደር የሚቃወሙትና በክፍለ አህጉሩ የእናት ቤተ ክርስቲያን እንቀስቃሴ መሪ ናቸው የሚባሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመግለጫው ባስተላለፈው ይፋዊ ጥሪ መሠረት፣ በገለልተኛ አስተዳደራዊ መዋቅር ከሚመሩ አብያተ ክርስቲያን ወገኖች ጋራ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን የሚመለሱበትንና የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚጠናከርበትን መልእክት በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው እንዲያስተላልፉ ይጠበቃል፡፡
ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና በስደት ከሚገኙ ሌሎች አባቶች ጋራ በፊታውራሪነት የጀመሩት የዕርቀ ሰላም ውይይት ወደፊት እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲጠናከር በምልአተ ጉባኤው የሰፈረውን መግለጫ ተፈጻሚነት ለመርዳት ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም የብዙዎች እምነትና ተስፋ ነው፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment