- የአቡነ ጢሞቴዎስ ዐምባገነንትና የኮሌጁ ጉዳይ ምልአተ ጉባኤውን ሲያወያይ ዋለ
- ሊቀ ጳጳሱ በበላይ ጠባቂነት ተወስነው የሽግግር ዋና ዲን እንዲሾም ሐሳብ ቀርቧል
- የኮሌጁ ሥራ አመራር ቦርድ ዛሬ ለምልአተ ጉባኤው ማብራሪያ ይሰጣል
የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከእናት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ወጥተው በገለልተኛ አስተዳደር ለሚመሩ አብያተ ክርስቲያን የአንድነት ጥሪ ሊያስተላልፍ ነው፡፡ ምልአተ ጉባኤው በትላንት፣ ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ውሎው የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና መዋቅር ከማጠናከር አንጻር በገለልተኛ አስተዳደር ለሚመሩ አብያተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ተግባራት መፈጸም እንደሚገባቸው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ በቀጥታ ይከታተለዋል በተባለው በዚሁ የቤተ ክርስቲያንን ማእከላዊ መዋቅር የማጠናከር ተግባር፣ ለገለልተኛ አብያተ ክርስቲያን የአንድነት ጥሪ የሚተላለፍ ሲኾን ጥሪውን የተቀበሉት አብያተ ክርስቲያን በሚያነሧቸው ጉዳዮች ላይ የሚወያይ ራሱን የቻለ አካል እንደሚቋቋም ተጠቁሟል፡፡ በውይይቱ በሚደረስበት መግባባት አብያተ ክርስቲያኑ በውጭ አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች አስተዳደር ሥር ተካተው የሚያስፈልጓቸው አገልግሎቶች ሁሉ በማእከል እንዲሟላላቸው መመሪያ መሰጠቱ ተገልጧል፡፡
ተጠሪነት ሳይኖር በራሳቸው ፈቃድ ቤተ ክርስቲያንን በገለልተኝነት የማቋቋም ኹኔታ ራሱን የቻለ መዋቅር መስሎ በይበልጥ የሚታየው በሰሜን አሜሪካ ነው፡፡ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት ጽ/ቤት በ፳፻፬ ዓ.ም. ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ በአሜሪካ ባሉት ሦስቱ አህጉረ ስብከት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚገኙት አብያተ ክርስቲያን ቁጥር 56 ያህል ብቻ ነው፡፡
በክፍለ አህጉሩ የተበተነውን ምእመን ለመሰብሰብ፣ መሠረታዊና እውነተኛ የኾነውን የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ለማስከበር ከባድ ውጣ ውረድ መታለፉን የገለጸው የሀ/ስብከቱ ሪፖርት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በቀጣይነት ለማጎልበት÷ በመዋቅርና በገለልተኛ አብያተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች በራሳቸው አነሣሽነትና ተቆርቋሪነት በመሠረቱት የአንድነት ማኅበር አማካይነት የሚደረገውን የወጣቶች እንቅስቃሴ መደገፍ፣ የካህናትን የእርስ በርስ ግንኙነትና የጋራ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮችን ማጠናከር፣ ከሀ/ስብከታቸው ውጭ እየመጡ ከመዋቅር ውጭ የኾኑ አብያተ ክርስቲያን የሚከፍቱና ክህነት የሚሰጡ ሊቃነ ጳጳሳት አንድነትን ከሚያናጋና ገለልተኝነትን ከሚያበረታታ ኢ-ቀኖናዊ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግን በመፍትሔነት አቅርቧል፡፡
በተያያዘ ዜና በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙት አባቶች ሲካሄድ ቆይቶ የተስተጓጎለው የዕርቀ ሰላም ሂደት እንዲቀጥል በአጀንዳ የተነጋገረው ምልአተ ጉባኤው፣ በስደት ያሉት አባቶች ፈቃድ ተጠይቆና አስፈላጊው ነገር ተሟልቶ ውይይቱ የሚቀጥልበት ኹኔታ እንዲመቻች መመሪያ መስጠቱ ተዘግቧል፡፡
ምልአተ ጉባኤው ስለ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ወቅታዊ ኹኔታ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ረዳት በንባብ የቀረበውን የአጣሪ አካል ሪፖርት አዳምጧል፡፡ ሪፖርቱ እንደተለመደው ከሥልጣናቸው እንዲገለሉ ቀደም ሲል ውሳኔ የተላለፈባቸውን የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስን ጠቅላይነትና ዐምባገነንነት እንዲሁም ብልሹ አስተዳደራቸው በኮሌጁ መልካም ስምና ቀጣይ ዕድገት ላይ የጋረጣቸውን አደጋዎች ዳግም ያረጋገጠ ነበር፡፡
በቅጥር፣ ዝውውር፣ ዕድገትና ስንብት የአንድ – ሰውን – ሁሉን – ወሳኝነት አጉልቶ ያወጣው ሪፖርቱ ኮሌጁ በአስተዳደሩ የቤተ ክርስቲያን ሳይኾን የግለሰብ ድርጅት እንደሚመስል አስረድቷል፡፡ በሦስት ሰዎች መከናወን ለሚገባው ሥራ የዘጠኝ ሰዎች ቅጥር የተካሄደበት፣ ሁለቱም የኮሌጁ ተሸከርካሪዎች ለሊቀ ጳጳሱ የግል ተግባር የመዋላቸው ኹኔታ በምሳሌነት ተጠቅሰዋል፡፡ በደቀ መዛሙርት አቀባበል ስድሳ ያህል ተማሪዎች ያቀረቧቸው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ (ESLCE) የትምህርት ማስረጃዎች ፎርጅድ መኾናቸው፣ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ‹‹ዲግሪ ተሠርቶ የሚሰጣቸው እንዳሉና ከእኒህም አንዳንዶቹ ከኢትዮጵያ ውጭ የሄዱ መኖራቸው›› ለምልአተ ጉባኤው አስደንጋጭ ነበር፡፡
በቀድሞው ፓትርያርክ ትእዛዝ የመንበረ ፓትርያርኩ የቁጥጥር አገልግሎት በኮሌጁ አዲሱ ሕንጻ ላይ ባካሄደው የኦዲት ምርመራ የ21 ሚልዮን ብር ሙስና መፈጸሙን አረጋግጦ ሳለ ምንም ርምጃ አልተወሰደም፡፡ የመምህራኑ ቅጥር፣ አያያዝ(በመኖርያ ቤት) እና ደመወዝ ኹኔታ ብልሹ እንደኾነና በሥራ ላይ ሥልጠና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ኮሌጁ የሠራው ሥራ አለመኖሩ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በቅርቡ በሊቀ ጳጳሱ የተደረገውንና በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ የተተቸውን የአካዳሚክ ምክትል ዲን ምደባ ሪፖርቱ ተቃውሟል፡፡
ሪፖርቱ የተጠቀሱትን ችግሮች በመሠረቱ ይፈታቸዋል ያላቸውን መፍትሔዎች በጠቆመበት ክፍሉ÷ የበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ በበላይ ጠባቂነት ብቻ እንዲቀመጡ፣ በአስተዳደርና የፋይናንስ እንቅስቃሴ ጉዳዮች ላይ እንዳይወስኑ፣ በምትኩ የሽግግር ዋና ዲን እንዲመደብ፣ በሊቀ ጳጳሱ የተደረገው አዲስ የአካዳሚክ ምክትል ዲን ምደባ ተሸሮ በምትኩ ሌላ እንዲሾም ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ተሟልቶና ጊዜውን ጠብቆ ከመሰብሰብ ጀምሮ ድክመት ያለበትና ለኮሌጁ የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችንና ስትራተጂዎችን ከማውጣት ይልቅ በሊቀ ጳጳሱ ተጽዕኖ ሥር ወድቆ የአስተዳደር ሥራም የሚሠራው ሥራ አመራር ቦርዱም ዳግም እንዲዋቀር ተብሏል፡፡
ለበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ከልክ ያለፈ ወዳጅነት በማሳየት ውሳኔዎች እንዳይፈጸሙ አድርገዋል ተብለው የሚወቀሱት ፓትርያርኩ ‹‹ሊቀ ጳጳሱ በበላይ ጠባቂነት ይወሰኑ›› የሚለውን ሐሳብ መደገፋቸው ተነግሯል፡፡ ምልአተ ጉባኤው ከሌሎች ቦርዶች በተለየ በኮሌጁ አስተዳደር ሳይቀር እየገባ ይወስናል የተባለውን የሥራ አመራር ቦርድ በዛሬው ዕለት ለማብራሪያ ጠርቷል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ከምልአተ ጉባኤው ስብሰባ እንዲወጡ ተደርጎ (ከስብሰባው በሚወጡበት ወቅት ችግር የበዛባቸው ፮ኛው ፓትርያርክ ከተሾሙ ወዲህ መኾኑን በመጥቀስ ፓትርያርኩን፣ ብፁዕ ዋና ጸሐፊውንና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን በብስጭት ወቅሰዋል) የታየው የኮሌጁ አጀንዳ በዛሬው ውሎው በሪፖርቱ ከተጠቆሙት መፍትሔዎች አንጻር የሥራ አመራር ቦርዱ ማብራሪያ ከተሰማ በኋላ መቋጫ እንደሚሰጠው ይጠበቃል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶየተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment