- ቅ/ሲኖዶስ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት እውነታውንና ትክክለኛውን የሚገልጽ ጽሑፍ እንዲዘጋጅ ለሊቃውንት ጉባኤው ትእዛዝ ሰጠ
- የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ለምልአተ ጉባኤው ስብሰባ የሰጠው ሽፋን ‹‹የጉርሻ ያህል ነው›› በሚል ተነቀፈ
- ‹‹ጉባኤው አገር አቀፍ ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍም ነው፤ የምንሰጠው ትምህርት ነው፤ የምንወድቀው የምንነሣው ስለ ሀገር ጉዳይ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን በዐይን የሚታይ በእጅ የሚጨበጥ ታሪክ ነው ያስረከበችው፤ በምን ምክንያት ነው[የአየር ሽፋኑ]ቀለል የሚለው›› /ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ/
- ‹‹ከባለሥልጣናት[ከመንግሥት] የምናገኛቸውን መልእክቶች እናስተላልፋለን፤ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትሩእናቶች በሆስፒታል እንዲወልዱ ደጋግማችኹ አስተላልፉን ብለው ነግረውን በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ሺሕ ሕዝብ በተሰበሰበበትና በየአጋጣሚው እናስተላልፋለን፤ እኛም እዚህ ስለ አገር ጉዳይ እንነጋገራለን፤ የምንነጋገረው ግን የሚተላለፈው የጉርሻ ያህል ነው፤ ለሕዝቡ እንዲተላለፍ እንጂ የሚዲያ ሱሰኛ ኾነን አይደለም፤ የሚነገረው ነገር ለሕዝቡ በአግባቡ ቢተላለፍ መልካም ነው›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በእያንዳንዱ አህጉረ ስብከት ሓላፊነት እንደሚካሄድ ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያን በሥሯ ያሉ ምእመኖቿን ቆጥራ መመዝገብ እንድትችል›› የሚካሄደው ይኸው ታላቅ አገራዊ ክንዋኔ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በሚያዘጋጀው ቅጽ አማካይነት እንደሚከናወን ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ የገለጸው፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በ፳፻፮ ዓ.ም. በጀት ዓመት የምእመናን ቆጠራ ለማካሄድ ከብር 29 ሚልዮን በላይ የበጀት ጥያቄ ለቅ/ሲኖዶስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ማቅረቡን መዘገባችን የሚታወስ ሲኾን ዛሬ በቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ እንደተጠቀሰው፣ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት የሚካሄደውን ቆጠራ ክንውን በቀጣይ የምንመለከተው ይኾናል፡፡