- መነኰሳቱ ገዳሙን ለቀው እንዲወጡ ዛቻና ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው ነው
- አስተዳደሩ ለመነኰሳቱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አልፈቀደም
- ‹‹ከዚህ ቦታ ባትመጡ ይሻል ነበር፤ ብትውሉ አታድሩም!›› /ጥቃት ፈጻሚዎቹ/
በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀ/ስብከት ወንጪ ወረዳ ሐሮ ወንጪ ቀበሌ በሚገኘው የሐሮ ወንጪ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው ጳጉሜ ፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ምሽት 5፡00 ላይ ወደ ገዳሙ ቅጽር በተወረወረው ቦምብ ነው፡፡
በገዳሙ የኪዳነ ምሕረት፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ዑራኤልና ቅድስት አርሴማ ታቦታት መኖራቸውን የገለጹት የገዳሙ አበምኔት መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገብረ ማርያም ኣብርሃ፣ የተወረወረው ቦምብ በገዳሙ ቅጽር ውስጥ ቢፈነዳም በመነኰሳቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ለዜና ሰዎች ተናግረዋል – ‹‹ቢፈነዳም እርሱ ሊቀ መልአኩ በተኣምሩ አንከባሎት ከልሎናልና ጉዳት አላደረሰብንም፡፡››