(ደጀ ሰላም ጥቅምት 30/2005 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 9/2012, READ THE NEWS IN PDF)፦በሃይማኖት ጉዳይ በተነሣባቸው ጥያቄ ምእመኑ ዓይናችሁን ላፈር ያላቸው ብዙ ሰዎች ቢኖሩም በተለይ በበጋሻውና በባልንጀሮቹ ላይ ጠበቅ ያለ አጀንዳ እንደተከፈተባቸው ለረዥም ጊዜ ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል። ጉዳዩ በቅዱስነታቸው እረፍት እና በመከካሉ በመጣው ጊዜ ክፍተት ተረሣ ቢመስልም “ይደር” ተባለ እንጂ “ይዘጋ” ስላልተባለ እነሆ ርዕሳችን አድርገነዋል። በድጋሚ። ከበጋሻው እንጀምር።
በጋሻው በሊቃውንት ጉባኤ የተያዘበት ጉዳይ ካለፈው ዓመት ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያደረለት የአንዳንድ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ሐዘኔታ በማትረፍ በአቋራጭ የቅ/ሲኖዶሱን ይቅርታ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ እንዳልሠራለት ታውቋል፡፡ የበጋሻው የኑፋቄ ንግግሮች የተሰራጨባቸውን ቪሲዲዎች እና መጻሕፍት መርምሮ ለምልአተ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብ ለማቅረብ የተቋቋመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ኮሚቴ “ግለሰቡ ለጥያቄ ተፈልጎ ስላልተገኘ ወደፊት ቀርቦ እንዲጠየቅና በሚሰጠው መልስ ጉዳዩ እንዲታይ በሚል አስተያየት ታልፏል” በማለቱ ጉዳዩ ሳይወሰንበት ለዚህ ዓመት ድኅረ አቡነ ጳውሎስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ተላልፎ የነበረ ቢኾንም ምልአተ ጉባኤው በሥራ ላይ በቆየባቸው ዐሥር ቀናት ከጥምር ኮሚቴው የቀረበለት ነገር አልነበረም፡፡