፩፦ ምክር
የሰው ልጅ ከልጅነት እስከ እውቀት፥ ከኲተት እስከ ሽበት ምክር ያስፈልገዋል። ጳጳስም ሆነ ካህን፥ ባዕለጸጋም ሆነ ደሀ፥ ባዕለ ሥልጣንም ሆነ ተርታ ሰው፥ ምክር የማያስፈልገው የለም። ማንም ይሁን ማን፥ በጎ ኅሊና ያለው መካሪ ከሌለው ከሚያለማው የሚያጠፋው ይበዛል። አበው፦ «መካሪ የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ፤» ያሉት ለዚህ ነው። ከዚያ በላይ ቢነግሥ እንኳ በኃይል እንጂ በፍቅር ሊነግሥ አይችልም። እያሠረ፥ እየገረፈ፥ እያፈናቀለ፥ እየገደለ፥ ግፍ በግፍ ይሆናል።
በጎ ምክርን የሚሰማ እንዳለ ሁሉ፥ የማይሰማም አለ። ቅዱስ ዳዊት ከበጎ ኅሊና የሚመነጭ ምክር ለሰው ሕይወት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ሲናገር «ለሚያደርጋት ሁሉ ምክር መልካም ናት፥ ምስጋናውም ለዘለዓለም ይኖራል።» ብሏል። መዝ ፩፻፲፥፲። ልጁ፥ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞንም፦ «አስተዋይ ግን ምክርን ገንዘብ ያደርጋል። ምሳሌንና የተሸሸገውን ነገር፥ የጠቢባንን ቃልና ዕንቆቅልሾችን ያውቃል። . . . ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፤ ለራስህ የክብር ዘውድ ለአንገትህም የወርቅ ድሪ ይሆንልሃል።» በማለት መስክሯል። ምሳ ፩፥፭-፱።