|
ትጉህ እና ቅን ለበጎቹ አሳቢ መሪ ይስጠን |
(ደጀ
ሰላም፤ መስከረም 9/2004 ዓ.ም፤ ሰምቴፕር 19/2012/ READ
THIS ARTICLE IN PDF)፡-
ከአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ማለፍ በኋላ በመንበረ ተክለ ሃይማኖት መቀመጥ የሚገባውን ቀጣይ አባት ከመሾም አስቀድሞ የአራተኛውን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ዕጣ ፈንታ መወሰን፣ ከዚህም ጋራ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት እንዲሁም የመዋቅር ማሻሻያ የሚመለከቱ ርምጃዎች መውሰድ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ኾኖ ወጥቷል፡፡ በአሜሪካው የሰላምና አንድነት ጉባኤ ከተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሂደት በተጨማሪ በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሥሓቅ የሚመራውና ከዐሥር ያላነሱ ልሂቃንን የያዘው የአገር ሽማግሌዎች ቡድን ሰሞኑን ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ በመወያየት በቅርቡ ቡድኑ በቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ የሚነጋገርበት ኹኔታ እንዲመቻች መደረጉ ተዘግቧል፡፡
በሌላ
በኩል የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባናል፤ የቅ/ሲኖዶስን የሰላምና የተቋማዊ ማሻሻያ ርምጃዎች በማገዝ ረገድ የበኩላችንንም ለማበርከት ተዘጋጅተናል የሚሉ የአገልጋዮችና ምእመናን ስብስቦችም ይበጃል በሚሏቸው ሐሳቦች ዙሪያ የሚመለከታቸውን አካላትና ሰፊውን ምእመን በተደራጀ መንገድ እያወያዩ ናቸው፤ ለውይይትና ግንዛቤ የሚረዱ ጽሑፎችም በተለያዩ መድረኮች እየቀረቡና እየተሠራጩ ይገኛሉ፡፡ ከእኒህም መካከል ውሉደ አበው ዘተዋሕዶ የተሰኘውና በዋናነት ለመረጃ፣ ለግንዛቤና ለውይይት የሚረዱ ጽሑፎችን መዘርጋት የጀመረው የአገልጋዮች መድረክ አንዱ ነው፡፡
መድረኩ
ባዘጋጀውና ለደጀ ሰላም መድረስ በጀመረው በዛሬው ሁለተኛ ጽሑፉ ከቀጣዩ ፓትርያሪክ ምርጫ አስቀድሞ መከናወን በሚገባቸውና ‹‹መንገድ ጠራጊዎች ናቸው›› በሚላቸው መሠረታዊ ሥራዎች ላይ ሐሳቡን በዝርዝር አቅርቧል፤ እኒህ መሠረታዊ የቅድመ ሢመተ ፓትርያሪክ ተግባራት ለቤተ ክርስቲያናችን፣ ለአገራችንና ለዓለም ሁሉ ያላቸውን በረከት በማመላከትም ተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው ይከራከራል፡፡ ደጀ ሰላማውያን ሁሉ በመድረኩ የጽሑፍ አበርክቶዎች ላይ ሐሳባቸውን በማቅረብ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ በባለቤትነት ለመወያየት እንችል ዘንድ ደጀ ሰላም ጥሪዋን ታቀርባለች፡፡
ቸር
ወሬ ያሰማን፣ አሜን።
+++