(ደጀ ሰላም፤ ሐምሌ 16/2004 ዓ.ም፤ ጁላይ 23/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በሙስና፣ ብኵንነት፣ ኑፋቄ እና ዐምባገነናዊ አሠራር የነቀዘው የአባ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና 20ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ዛሬ ምሽት ለሁለተኛ ጊዜ በሼራተን አዲስ ይከበራል። የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እና ራእይ ለትውልድ /Vision for Generation/ የተባለው አካል የጥቅም ትስስር የፈጠሩበት የሼራተኑ በዓለ ሢመት ዝግጅት በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ይኹን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት አይታወቅም።
የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአብያተ እምነት መሪዎች፣ አምባሳደሮችና ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ እስከ 1500 እንግዶች ይታደሙበታል በተባለው ይኸው ዝግጅት ከጥቅም ትስስር ባሻገር÷ በግንቦቱ ቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ እና ውሳኔዎች ክፉኛ የተጋለጠውን የአባ ጳውሎስን ማንነት ለማደስ የታሰበበት ‹የሕዝብ ግንኙነት› ሥራ እንደኾነ ተጠቁሟል። በበዓለ ሢመቱ አከባበር የቀደሙት ፓትርያርኮች መልካም ስምና ዝና በተለያዩ ስልቶች እየተንኳሰሰ በምትኩ በሙስና፣ ኑፋቄ እና ዐምባገነናዊ አሠራር የተበሳበሰው የአባ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና የሥራ ክንውን ብቻ “በወደር የለሽነት” /በእንግሊዝኛው የበዓለ ሢመት ኅትመት ላይ እንደተገለጸው - ‘unparalleled efforts/ እንደ ግለሰብ መሞገሱ ብዙዎችን አሳዝኗል።