ከዚህም ከዚያም




ጸናጽል

ጸናጽል በቁሙ ሻኩራ ቃጭል ማለት ነው፡፡ ጸናጽል አበው እግዚአብሔርን ያመሰገኑበት የተቀደሰ ንዋይ የመዝሙር መሳሪያ ነው፡፡፩ዜና ፲፫፥፰ ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጽልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር፡፡
መዝ ፲፭፥፭ ድምጹ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፡፡
፩ ቆሮ ፲፫፥፩ በሰዎችና በመላዕክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮህ ናስ ወይም እንደሚንሸዋሸው ጸናጽል ሆኛለው፡፡
አሠራሩና ምሳሌያዊ ትርጉሙ
ጸናጽል የሀ ቅር ጽ ኖሮት ከብር ከናስ ከወርቅ ይሠራል፡፡ በሀ ቅርጽ መሐል ሁለት ዘንጎች አግድም እንዲኖሩት ይደረጋል፡፡ በዘንጎቹም ላይ ቅጠሎቹ/ሻኮራዎቹ/ ይንጠለጠላሉ፡፡ እነዚህ ሻኮራዎች ቁጥራቸው የታወቀና የተወሰነ ነው፡፡ ከላይ ቀስት ሚመስል ደጋን ይሠራል፡፡ ሀ ቅርጽ ያለው ብር ናስ …. መያዣ እንዲሆን ከታች እጀታ ይደረግለታል፡፡

1)      ሁለቱ ዓምዶች የሁለቱ ኪዳናት /ብሉይና ሐዲስ ኪዳን/ ምሳሌ ናቸው፡፡ ጸናጽሉን የሚያቆሙትና የሚያጸኑት ሁለቱ ዓምዶች እንደሆኑ ሃይማኖትም የሚጸናው በብሉይና በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ነው፡፡
2)      ሁለቱ ጋድሞች በሁለቱ ዓምዶች መካከል የሚዘረጉ ሻኩራዎቹን የሚይዝ ሁለት ጋድሞች አባታችን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ተኝቶ ሳለ በሕልሙ ባየው መላዕክት ሲወጡበት ሲወርዱበት የነበረው የብርሃን መሰላል ምሳሌ ነው፡፡ ኦሪ ዘፍ ፳፰፥፲፪-፲፫/2812-13/

           እነዚህ ጋድሞች ሁለት የሆኑበት ምሳሌያዊ ትርጉም አላቸው



ሀ)      የፍቅረ ቢጽና የፍቅረ እግዚአብሔር ምሳሌዎች ናቸው፡- ቅዱሳን መላዕክት ጋድሞቹን እየረገጡ ወደ ሰማይ ሲወጡ ወደ ምድር ሲወርዱ እንደነበረ አባታችን ያዕቆብ አይቷል፡፡ ሰውም ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ አድርጎ ወደ መንግስተ ሰማያት እንዲገባ ለማጠየቅ ጋድሞቹ ሁለት ሆነዋል፡፡
ለ)      የደቂቀ አዳምና የደቂቀ መላዕክት ምሳሌዎች ናቸው፡- በጋድሞቹ ላይ እየወጡና እወረዱ የታዩት መላዕክት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ይዘምሩ ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳን ከቅዱሳት መላዕክት ጋር ደቂቀ አዳም በአንድነት ሆነው እንዲያመሰግኑ ለማጠየቅ የመሰላሉ ጋድሞች ሁለት ሆነዋል፡፡
ሐ)      የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ናቸው፡- ሁለቱ ጋድሞች ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሄር የሚያደርሱ መሸጋገሪያ ድልድዬች ናቸው፡፡ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻህፍትም የመንግስተ ሰማያት መውረሻ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገሪያ ስለሆኑ ጋድሞቹ በእነርሱ ተመስለዋል፡፡

    ቅጠሎቹ ወይም እንክብሎቹ፡- የቅዱሳን መላዕክት ምሳሌ ናቸው፡፡ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ባየው የብርሃን መሰላል ላይ  ወጡና ሲወርዱ የነበሩት መላዕክትን እንድናስብ በጋድሞቹ ላይ ቅጠሎቹን ይደረጋሉ፡፡ ጸናጽሉ ሲወዛወዝና ቅጠሎቹ የሚሰጡትን ድምጽ ስንሰማ ቅዱሳን መላዕክቱን በመውጣትና በመውረድ ማመስገናቸውን እናስብበታለን፡፡

  •        ቅጠሎቹ ወዲያና ወዲህ መባሉ የጌታችን በአይሁድ መንገላታት ምሳሌ ነው፡፡


3)      የቅጠሎቹ ቁጥር፡- በጋድሞቹ የሚደረጉ ቅጠሎች ቁጥር ሦስት ከሆ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ/ የሥላሴ/ ምሳሌ ናቸው አምስት ከሆነ የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር ስድስት ከሆኑ የስድስቱ ቃላተ ወንጌል ሰባት ሲሆኑ የሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች ይሆናሉ፡፡
4)      ቀስተ ደመና -በጸናጽሉ ላይ የምናገኘው ቀስተ ደመና የሚመስለው ክፍል የኖህ ቃል ኪዳን ምሳሌ ነው፡፡ እግዚአብሔር አለ፡- በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ለዘለዓለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፡፡ ቀስቴን በደመና አድርጌያለው፡፡ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል፡፡ ኦሪ ዘፍ ፱፥፲፪



------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“ተሀድሶን” ጠርገን ሳናስወጣ “ተዋህዶ” የሚሉ ደግሞ ብቅ ብለዋል


(አንድ አድርገን የካቲት 28 2005 ዓ.ም )፡- ከአመት በፊት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልጀርባ  ኤልያስ ወደ ምድር ወርዷል  ትክክለኛ ሰንበት ቅዳሜ እንጂ እሁድ አይደለም  “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች” መባል አንፈልግም እኛ የኢትዮጵያ ተዋህዶ አማኞች” ነን “ኦርቶዶክስ”የሚለው ስም ተለጥፎብን ነው እንጂ እኛን የሚገልጽ አይደለም ፤  የአሁኗ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶእምነት ስርዓተ ቤተክርስቲያን አንዳድን ቦታ ላይ ትክክል አይደለችም  ስለ አማላጅነትና መሰል ከኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ጋር የሚጣረስ ሃሳብ ያላቸው ቡድኖች በአሁኑ ሰዓት በመሀል አዲስ አበባ “ማኅበረ ስላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ አሃቲ የሰማይ ጉባኤ ዘቅድስት ቤተክርስቲያን ቅድመ መንበሩ ለእግዚነ ወእመፍጥረት ወላዲተ አምላክ” በሚል ስም ምእመኑን ግራ እያጋቡት ይገኛሉ፡፡

 እነዚህ ቡድኖች  ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስንእልክላችኋለሁ።” ትንቢተ ሚልክያስ  4ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናናል” የማርቆስወንጌል 9 12 የሚሉትን የመጽፍ ቅዱስ ቃል መሰረት በማድረግ ነብዩ ኤልያስ ወደ ምድር ጳግሜ 5 2003. እንደመጣ አብዝተው ይሰብካሉ ፡፡ ቦታው መሃል አራት ኪሎ ሲሆን በርካቶችን በተለያዩ በራሪ ወረቀቶችበመሳብ ላይ ይገኛሉ ፡፡  ቦታው ድረስ ሄደን እንደተመለከትነው አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞንን የመሰሉ አርቲስቶች ቆብ ያጠለቁ መነኮሳትና ለማገልገል የሚፋጠኑ ወጣቶች በቦታው ላይ መመልከት ችለናል ፡፡ ተሀድሶያውያንም ሆኑ አሁን ላይ “ተዋሕዶ” ብለው ራሳቸውን ከእኛ ጋር እጅጉን በማመሳሰል የተነሱት ሰዎች መጨረሻቸው መንጋውን ከበረቱ ማስወጣት ነው፡፡ አሁን ላይ “ተዋሕዶ” የሚለውን ትርጉም ከአባቶች እንዳገኝነው በማለት የራሳቸውን ፍልስፍና ምዕመኑን እየጋቱት ይገኛሉ ፤ ጥቂቶች እስከ አሁን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መባል አልነበረብንም በማለት የጉባኤያቸው ተካፋይ መሆን ጀምረዋል ፡፡ እያየን ያለነው ነገር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞችን አንገታቸው ላይ የሚያስሩት ክር ትክክል አይደለም ፤ “ከሰማይ የተሰጠው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ክር ነው” በማለት ምዕመኑን የበፊቱን እያስወለቁ አዲሱን የራሳቸውን ክር እያጠለቁለት ይገኛሉ… ይሄ ነገር ዛሬ ዝም ከተባለ ነገ በዝተው የባሰ ቀውስ እንዳያመጡም ስጋት አለን …ለማንኛውም በዚህ አመለካከት  የተጠመቀችው ለምስክርነትም በቃው የምትለው አርቲስት ጀማነሽ ምን እንደምትል ከየካቲት ወር እትም ከሚሺሪያ መጽሄት ጋር ያደረገችው ሙሉ ቃለ መጠይቅ ብሎጋችን ላይ ለጥፈንልዎታል ያንብቡት….

ጥቂት ከቃለ መጠይቁ የተወሰደ
  • ኦርቶዶክስ ሽፋን ነው፡፡ ቅባት ፤ ጸጋ ፤ ዘጠኝ መለኮት እያሉ በግድ አብረው ኦርቶዶክስ በሚል ሰንሰለት ከተዋሕዶ ጋር ጠፍረው አስረው አንድ ላይ ያስቀመጧቸው እምነቶች መሆናቸውን ተረድቻለሁ፡፡
  • ኦርቶዶክስ ማለት ጸጋን ቅባትንም ዘጠኝ መለኮትንም የሚጠቀልል ከሆነ እኔ ኦርቶዶክስ አይደለሁም ፡፡ አልፈልገውም ፤ አልቀበል፤ እኔ ተዋህዶ ብቻ ነኝ፡፡
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲባል ቀጥተኛዋ ተዋሕዶ  የሚሉ ስለሚመስለኝ እኔም በዚያ ስም ራሴን ስጠራ ነው የኖርኩትኝ፡፡ በቅዱስ ኤልያስ አዋጅ ላይ ነው ያየሁት ፡፡ የቅዱስ ኤልያስ አዋጅም “እነዚህ እምነቶች የክርስትና እምነት ስላሆኑ ከተዋህዶ ጋር አንድነት ስለሌላቸው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሱ ንስጥሮስን እንዳወገዙ ፤ አርዮስን እንዳወገዙ በእምነትም በዶግማም ስለማይመሳሰል አውግዛችሁ ልትለዩ ይገባል” የሚል ታላቅ አዋጅ ነው ያየሁት ፡፡ ይህን ግን ሲኖዶሱ አልተቀበለውም፡፡
  • ከአሁን ወዲያ ደግሞ እውነተኛውን ነገር እስካወቅን ድረስ  አንደ አባቶቻችን “የለም ፤ አይሆንም ፤ አንድ አይደለንም” ብሎ መቆም ደግሞ የኛ ፋንታ ነው፡፡
  • ተዋሕዶ ነን ብላችሁ ልዩነት ስትፈጥሩ ተሃድሶ እንደሚባለው ሊፈረጅ ይችላል የሚል ስጋት የለሽም? (ከጋዜጠኛ የቀረበላት ጥያቄ)
  • ቅባት ጸጋ የሚባሉት እኛን ተዋህዶ በመሆናችን የከሰሱን እና ወንጀለኛ የደረጉን ናቸው ፤ በሙሉ ገዳም ውስጠ ያሉት በዚህ ተይዘዋል ፤ ጥቂት ተዋህዶ አማኞች  በስቃይ የሚኖሩ አሉ፡፡
  • በአሁን ጊዜ ብዙ ሃይማኖቶች አሉ ፤ እውነት ግን ያለው በአንድ መንገድ ብቻ ነው ፤ አሷምተዋህዶ ናት፡፡
  • ስንት ገዳም ገብቼ የስንት አባቶችን መስቀል ተሳልሜአለሁ ፡፡ ሳስበው ይዘገንነኛል ፡፡ ዋልድባን የሚያህል ቅዱስ ገዳም ነው በእንደዚህ አይነቶች ተሞልቶ ያገኝሁት፡፡ ዋልድባን የሚያህል የቅዱሳን አባቶች መቀመጫ ገዳም “ዘጠኝ መለኮት” የሚሉ መናፍቃን ግማሹን ይዘው እንዳሉበት አላውቅም ነበር፡፡
  • ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችን ልብ ወደ አባቶች ይመልስ ዘንድ  ቅዱስ ኤልያስን እልክላችኋለሁ” ይላል አሁን ኤልያስ የመጣው ይህን ሊገልጥ ነው፡፡
  • እግዚአብሔር ከዚህ መስመር (ተዋሕዶ) ከሚያስወጣኝ ቢገለኝ እመርጣለሁ፡፡
  • ሶሪያ ትንቢተ ኢሳያስ ላይ እንደሚላት እየወደመች ነው ፤ አሜሪካ እንደምትጠፋ ራዕይ ላይ ተጽፏል
TO READ IN PDF CLICK HERE


ወደ ኮምፒዩተርዎ ሴቭ በማድረግ ያንቡት

--------------------------------------------------------------------------------------------------------

በወቅታዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የቅ/ሲኖዶሱ አባላት አቅዋም ምን ይመስላል?

  • ‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› የሚሉ አባቶች በአቋም ተጠናክረዋል፤ በቁጥር ጨምረዋል
  • የምልአተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ ከቀትር በኋላ ውይይቱን ይቀጥላል
አቋም መያዝ የመራጭ (ምርጫ ያለው) ግለሰብ ወይም ቡድን መብት ነው፡፡ ከምን አንጻር ወይም ለምን ዓላማ ከሚለው በመነሣት አቋሙን ማሔስ ወይም መተንተን ደግሞ የወደረኞች፣ የተገዳዳሪዎች፣ የተሟጋቾች፣ የተበላላጮች ጠባይዕ ከእነርሱም አልፎ የተመልካቾች መብትና ነጻነት ነው፡፡
በተነሣንበት ርእሰ ጉዳይ÷ ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ቅድሚያ የሚሰጡ አባቶችና  ወገኖች ለአቋማቸው ሥልጡንና ሥዩም (entitled) ቢኾኑም ‹‹ከምርጫው ይልቅ ለሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተን የልዩነቱን ምዕራፍ እንዝጋ፤ የዕርቀ ሰላም ሂደቱን ፍጻሜ እንጠብቅ፤ ውጤቱን እንይ፤ ለውጤቱም እንሥራ›› የሚሉ አባቶችና ወገኖች የያዙትን አቋምና የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ‹‹የብዙኀን ዐምባገነንት ነው፤ የሥልጣን ጥማትና የተቃዋሚ ፖሊቲከኞች ሽፋን ነው›› ብለው ሊተቹ ይችላሉ፡፡ እኒህም እነኛን ‹‹ዕርቅንና ሰላምን የጠሉ፣ ሥልጣን የሚወዱ፣ ለመንግሥት ተጽዕኖ ያደሩ›› ቢሏቸው ያው ትችት ነው፡፡ ግና ቁምነገሩ የታሪክ ስሕተቶችን ከማረም፣ ለዘመኑን ለመጪው ትውልድ ጠንካራ ቤተ ክርስቲያንን ከማቆየት አንጻር የሚበጀው የቱ ነው የሚለውን በትክክልና በአግባቡ መመለስ ነው፡፡
ሐራውያን እይታ ‹‹ከምርጫው ይልቅ ለሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥተን የልዩነቱን ምዕራፍ እንዝጋ፤ የዕርቀ ሰላም ሂደቱን ፍጻሜ እንጠብቅ፤ ውጤቱን እንይ፤ ለውጤቱም እንሥራ›› የሚለው አቋም የብዙኀን አቋም ነው፡፡ መሠረቱ በደልን እየተዉ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አንድነት፣ መንፈሳዊ ሕይወትና ተቋማዊ ጥንካሬ መጨነቅ ነውና ‹‹ከብዙኀን ዐምባገነንነት›› ሊመነጭ አይችልም፡፡ ከተባለም እንደ ነገሩ አግባብነት የአንዱ ሰው (የጥቂቶች) ስለ ብዙኀን ‹መሞት›፣ ለብዙኀን ፍላጎት መገዛት ክርስቶሳዊነት (ዮሐ.18÷14) ነውና የሚነቀፍ አይኾንም፡፡ እውነታው÷ በአቋማቸው ያጽናቸው ከቁጥርም አያጉድላቸው እንጂ ‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› የሚሉ አባቶች በአቋም ተጠናክረዋል፤ በቁጥርም መጨመራቸው ነው፡፡
አሁን ጎልተው የወጡና ከሞላ ጎደል በሁለት ተጠቃለው ሊወሰዱ የሚችሉ ወቅታዊ አጀንዳዎች አሉ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የቅ/ሲኖዶሱ አባላት ከሰጡት አስተያየትና ካንጸባረቁት አቋም በመነሣት ሐራውያን ምንጮች ባካሄዱት የአቋም ማመዛዘን (በሂደት ሊታይ የሚችለው የአቋም ሽግሽግ የሚጠበቅ ኾኖ) ይህ ጽሑፍ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በአባላቱ ዘንድ የሚታየውን አሰላለፍ/አቅዋም እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፡፡
1)  ለፓትርያሪክ ምርጫው የዕርቀ ሰላሙን ውጤት መጠበቅ አያስፈልገንም፤ የዕርቀ ሰላም ሂደቱ ከፓትርያሪክ ምርጫው ጎን ለጎን ሊካሄድ ይችላል፤
  • ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል (በአሁኑ ወቅት ለፓትርያሪክ ምርጫው ቅድሚያ ሰጥቶ ከመሥራት አኳያ በግልጽም በስውርም ከሚከናወኑት ተግባራት ሁሉ ጋራ ተያይዞ ስማቸው የሚነሣ አባት ናቸው፤ ‹‹ባለራእይና ዘመናዊ አባት ናቸው›› የሚሏቸው ቀራቢዎቻቸው ፍላጎት እንደሌላቸው ቢናገሩም ሌሎች ወገኖች በቢሯቸው አካባቢ የሚታየውን የብዙዎች ወጣ ገባ ማለትና በተለያዩ መድረኰች የሚያደርጓቸውን ንቁ ተሳትፎ በማገናዘብ የምርጫ ዘመቻ መሰል ነገር መጀመራቸውን ይናገራሉ)
  • ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
    ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
  • ብፁዕ አቡነ አብርሃም (የሰላም ድርድሩ/ንግግሩ ከፓትርያሪክ ምርጫው ጋራ ግንኙነት የለውም፤ ሁለቱ አቋሞች አይጫረቱም/አይነጻጸሩም/፤ ድርድራችንም ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋራ ብቻ መኾን ይገባዋል በሚለው አቋማቸው እና በሰላምና አንድነት ጉባኤው ላይ በሚሰነዝሯቸው ሒሶች ይታወቃሉ)
  • ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ (ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ የሚሉ አባቶችን በሃይለ ቃል በማሸማቀቅና ከምርጫው አኳያ የሚከናወኑ ተግባራት እንዲፋጠኑ እየሠሩ ናቸው፤ ለረጅም ጊዜ በቆዩበት ሀገረ ስብከት አጥጋቢ ተግባር ባለማከናወናቸው ብቻ ሳይኾን በችግሮች አፈታታቸው የሚተቿቸው ቀራቢዎቻቸው ለፓትርያሪክነት በዕጩነት እንደሚቀርቡ ከዚህም በላይ ቀጣዩ ፓትርያሪክ ሊኾኑ እንደሚችሉ በመስማታቸው ብቻ እንኳ ይሣቀቃሉ)
  • ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ (በአስመራጭ ኮሚቴው አባላት አሠያየም ዋነኛ ሚና ተጫውተዋል)
  • ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ (ዕርቀ ሰላሙ ሢመተ ጵጵስናቸውን ጥያቄ ውስጥ እንዳያያስገባው ይሰጋሉ)
  • ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ
  • ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ
  • ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም
  • ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን እንዲጀምር ማሳሰቢያ የተሰጠበትን ደብዳቤ የፈረሙ፣ ከሰሞኑም የ6ው ፓትርያሪክ ምርጫ በአጭር ጊዜ እንዲካሄድ እየተደረገ ለሚገኘው እንቅስቃሴ አስተዳደራዊ ድጋፍ እየሰጡ የሚገኙ ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ (ቀደም ባሉት ዓመታት ለአራተኛው ፓትርያሪክ በጻፉት ደብዳቤ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሲባል ‹‹ብዙ ነገር እንዲታገሡ›› ተማፅነዋቸው ነበር፡፡ አሁን በያዙት አቋም ደግሞ የውጭዎቹን አባቶች ‹‹ሰላም አይፈልጉም፤ ፖሊቲከኞች ናቸው፤ ወደ ምርጫው እንግባ›› የሚል አቋም ይዘዋል፤ ኾኖም በአስመራጭ ኮሚቴ አባልነታቸው ላይ ያላቸው አቋም ብዙም አስተማማኝ አይደለም፡፡)
2)  ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት የዕርቀ ሰላሙን ፍጻሜ ማየት፣ ውጤቱን መጠበቅ፣ ለውጤታማነቱም መሥራት ይገባናል፡፡ አጋጣሚው ካለፈው ተምረንና በታሪክ ማኅደር አስቀምጠን ለዘመናችንና ለቀጣዩ ትውልድ በአስተዳደር የተከፋፈለች ሳይኾን አንዲት ቤተ ክርስቲያንን የምናስረክብበት ነው፡፡ ይህን ሳናደርግ ወደ ፓትርያሪክ ምርጫ የምንገባውና ፓትርያሪክ የምንሾመው ለማን ነው? የቤተ ክርስቲያን መከፋፈል የከፋ ይኾናል፤
  • ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ (በአሜሪካ ተልእኳቸው የሰላምና አንድነት ጉባኤውን መግለጫ በመቃወም በዕርቀ ሰላም ልኡካኑ መካከል‹‹የተቃውሞ መግለጫ እንስጥ፤ የለም! አገር ቤት እስክንገባ እንቆይ›› የሚል ክርክር በተነሣበት ወቅት በንቡረ እድ ኤልያስ የተሞከረውን የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን በአቋም የመከፋፈል ተንኰል በመቋቋም የልኡኩን አንድነት ያስጠበቁ ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ (ከዕርቀ ሰላም ልኡካኑ አባላት መካከል በልዩ ኹኔታ ጫና እየተደረገባቸው የሚገኙ፣ በዛሬው የአስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባም ሕመማቸው እስኪቀሰቀስ ድረስ አበክረው ለዕርቀ ሰላሙ ሲናገሩ የዋሉ ናቸው)
    አቡነ ቀውስጦስ
    አቡነ ቀውስጦስ
  • ብፁዕ አቡነ ገሪማ (ለዕርቀ ሰላም ጉባኤው ወደ አሜሪካ ተልከው አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን በዚያው ኾነው በሰሙ ጊዜ እንባቸውን ማፍሰሳቸው ይነገራል)
  • ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ (‹‹የላኳቸው ሳይመለሱ በመልእክቱ ላይ አልወስንም›› በሚለው ዝነኛ ንግግራቸው አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን የተቃወሙ፣ የኮሚቴው አባል ኾነው መምረጣቸውንም ያልተቀበሉ አባት ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘኢየሩሳሌም (በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት እያሉ ዕርቀ ሰላምን አስመልክቶ ለአቡነ ጳውሎስ ደብዳቤ የጻፉ፣ ከዕርቀ ሰላም ሐሳብ አመንጪዎች መካከል ስማቸው የሚጠቀስ አባት ናቸው፡፡ ለፓትርያሪክ ምርጫው በዕጩነት እንዲቀርቡ –በቀጥተኛ አነጋገር ቀጣዩ ፓትርያሪክ እንዲኾኑ – የመንግሥትና እንደ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ያሉት አባቶች ግልጽ ድጋፍ ያላቸው ቢኾኑም ስለእርሳቸው አቋም በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፤ ሌሎች አባቶች ብፁዕነታቸው አሜሪካዊ ዜግነት መያዛቸውንና ዕድሜያቸውን በመጥቀስ – በአንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 4 ከ50 ያላነሰ ከ70 ያልበለጠ ስለሚል – ዕጩነታቸውን ይቃወማሉ)
  • ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ (በዕርቀ ሰላሙ ላይ ግልጽ አቋም እንዲያዝ ያሳሰቡ ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ (‹‹እግዚአብሔርን ዕድሜ እለምነዋለኹ፣ ቤተ ክርስቲያን አንድ ኾና እስከማይ፤ ከዚያ በኋላ መኖርን አልሻም›› በሚል ተምኔታቸው ይታወቃሉ፡፡
  • ብፁዕ አቡነ ሉቃስ (‹‹ለዘመኑና ለተከታዩ ትውልድ የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን አናወርስም፤ ሰላምን ለማምጣት መታገሥ ይገባናል›› በሚለው ንግግራቸው ይታወቃሉ፡፡ በታኅሣሡ ስብሰባ የዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ ሳይታይ የአስመራጭ ኮሚቴውን መሠየም ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ጋራ በጽኑ ተቃውመዋል፤ በመጨረሻም ከስብሰባው ሂደት ራሳቸውን አግልለዋል፤ በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ ጳጳሳት በግልጽ ተዘልፈዋል)
     ብፁዕ አቡነ ሉቃስ
    ብፁዕ አቡነ ሉቃስ
  • ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ (ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ይሰጥ በሚለው አቋማቸው አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን ተቃውመዋል፤ በአባልነት መመረጣቸውንም አልተቀበሉትም)
  • ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል (በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነታቸው ባላቸው ሓላፊነት ዕርቀ ሰላሙ ከፓትርያሪክ ምርጫው በትይዩ/በተጓዳኝ እንደሚካሄድ ቢገልጹም በታኅሣሡ ስብሰባ የዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜና ውጤት ዕድል እንዲሰጠው፣ በአንድነትም ወደ ምርጫው እንዲገባ ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ ጋራ በጽኑ ተከራክረዋል፤ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን በግልጽ ተቃውመዋል)
  • ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ (ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት የዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ እንዲታይ፣ ምርጫው በተረጋጋ መንፈስና በአንድነት ለቤተ ክርስቲያን የሚኾናትን ደገኛ አባት በመምረጥ እንዲካሄድ የሚያሳስቡ አባት ናቸው፤ ከዚህ በቀር ‹‹አላሿሹምም›› በሚለው አነጋገራቸው የሚታወቁ ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (በውጭ ያሉት አባቶች ለፓትርያሪክ ምርጫው የሚያስፈልጉ በመኾኑ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ መስጠት፣ ውጤቱን መጠበቅና ለውጤቱም መሥራት እንደሚገባ ያሳሰቡ፣ ወትዋቾችን የገሠጹና ያባረሩ አባት ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ዳንኤል (በውጭ ያሉት አባቶች ለፓትርያሪክ ምርጫው የሚያስፈልጉ በመኾኑ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ መስጠት፣ ውጤቱን መጠበቅና ለውጤቱም መሥራት እንደሚገባ ያሳሰቡ፣ ወትዋቾችንና የሥልጣን ጥመኞችን ጭምር የገሠጹ ‹እንጃልህ› ያሉ አባት ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል (የቅ/ሲኖዶሱ አስመራጭ ኮሚቴ የመሠየም አጀንዳ ያልተመከረበት መኾኑን፣ ኮሚቴው እንዲሠየም መወሰኑም የዕርቅና ሰላም ጉባኤውን ሂደት የሚያስተጓጉል በመኾኑ ከተጨማሪ ርምጃ መቆጠብ እንደሚገባ በሚዲያ በግልጽ አሳስበዋል)
  • ብፁዕ አቡነ ቶማስ (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ የሚለውን አቋም በግልጽ የሚያስተጋቡ አባት ናቸው)
  • ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
  • ብፁዕ አቡነ ኄኖክ
  • ብፁዕ አቡነ እንድርያስ
3)  አቋማቸው ለጊዜው አልተገለጸም፤ አይታወቅም፡፡ በስብሰባዎች ላይም በተሳትፎ ብዙም አይታወቁም፡፡ ከሁለቱ አቋሞች ወደ አንዱ በተለይም ለዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ ቅድሚያ ከመስጠት አኳያ አቋም እንደሚይዙ ወይም አቋማቸውን ግልጽ እንደሚያደርጉ ተስፋ ይደረጋል፡፡
  • ብፁዕ አቡነ ስምዖን
  • ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ (ከአኗኗራቸው፣ ከልምዳቸውና ከትምህርት ዝግጅታቸው አኳያ በቀጣዩ ፓትርያሪክ ምርጫ በዕጩነት እንደሚታሰቡ ይነገርላቸዋል)
  • ብፁዕ አቡነ ዮናስ
  • ብፁዕ አቡነ ያሬድ
  • ብፁዕ አቡነ ሰላማ
  • ብፁዕ አቡነ ኤልያስ
  • ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
  • ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም
  • ብፁዕ አቡነ በርቶሎሜዎስ
  • ብፁዕ አቡነ ማርቆስ
  • ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘካናዳ

----------------------------------------------------------------------------------------------------------
የሴት ራስ - ወንድ
ከመምህር ብርሃኑ አድማሴ የፌስ ቡክ ፔጅ የተገኘ ነው፣ ያስተመራል ይመክራል ብለን ስላሰብን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፥ መልካም ንባብ. . .

እንደምን ሰነበታችሁ፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ በመጥፋቴ ይቅርታ እየጠየቅሁ ለጊዜዉ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የሃይማኖት ዐምድ ‹‹ሃይማኖት እና ሴቶች›› በሚለዉ የመወያያ ርእሰ ጉዳይ ላይ ከእኛ እምነት አንጻር ያቀረብኳትን ትንሽ መጣጥፍ እነሆ ብያለሁ፡፡



ከዚህ በታች ያሉት ሁለት የቪዲዮ ትምህርቶች ወቅታዊ እና ጥሩ አስተማሪ ነው ብለን ስላመንን ተከታተሉት፣ ሁለት ክፍሎች ያሉት በዲ/ን ዳንኤል ክብረት ሰባኪ ወንጌል የቀረቡ ናቸው፥ ርዕሱ ""የሲኦል ደጆችም አይችሉአትም።" ማቴ ፲፮ ፥ ፲፰ "ልቦናችንን ከፍተን ለመከታተል አምላከችን ይርዳን አሜን

ክፍል ፩



                                ክፍል ፪ እና የመጨረሻው ክፍል ነው ተከታተሉት


ኦርቶዶክስ መልስ አላት በሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ



የአጽዋማት ሥርዐት

ክፍል ሁለት

እነርሱም
ሀ. የመጀመሪያው ጾም፣ ዐቢይ ጾም ወይም ሁዳዴ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጦመው የአርባ ቀን ጦም ነው፡፡ (ማቴ፡4፣1) ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጦሙታል፡፡ ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት (55 ቀኖች) አሉት፡፡ ከእነዚህም ቀኖች ውስጥ ሰባት ቅዳሜ ስምንት እሑድ ይገኛሉ፡፡ ዐሥራ አምስት ቀን ማለት ነው፡፡ ከጥሉላት እንጂ ከእህልና ከውሃ ስለማይጦም የጦሙ ወራት አርባ ቀን ብቻ ነው፡፡ ይህም በጥንታዊትዋ ቤተ ክርስቲያን የነበረ ሥርዐት ነው፡፡ ለምሳሌ በ384 ገደማ ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም ከእስፓኝ ወደ ኢየሩሳሌም ረዥም ጉዞ የሄደችው (Egeria) ኤጌሪያ የተባለችው ሴት የተሳላሚ ጉዞ በሚለው መጽሐፏ (Peregrinatioed Loca sancta) እንደጐበኘችና የጥንት ክርስቲያኖችም በዚህ አቈጣጠር ሲቈጥሩ ማየቷን ጽፋለች፤ የቆጵሮሱ ኤጲስ ቆጶስ ኤጲፋንዮስም በዚህ አቈጣጠር ይቈጥር ነበር ፡፡ (ፒ.ጂ.42 ሽህ 828) ሌሎች ደግሞ የመጀመሪያውንና የመጨረሻውን ሳምንት ለይተው ይቈጥራሉ፡፡ ለምሳሌም የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሕርቃል /ኤራቅሊዮስ/ የቢዛንታይን ንጉሥ ነበር፡፡ (714 ዓ.ም.) ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት አለው፤ በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደፋርስ ዘምቶ መስቀሉን ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶአል፡፡ በዚህ ምክንያት ክርስቲያኖች ደስ ብሎአቸው ለስሙ መታሰቢያ ይህን የጾም ሳምንት በቀኖና ውስጥ አስገቡለት እየተባለ ይነገራል፡፡ ግሪኮች ግን ጾመ ሕርቃል የሚባለውን ነገር አያውቁም፤ በዚህ ሳምንት ከእንቁላል፣ ከአይብና ከዓሣ በቀር ሥጋ አይበላም ክልክል ነው፡፡ ጾም መሆኑንም ይናገራሉ፤ ከላይ የተጠቀሱትን መባልዕት መብላታቸውም በተድላ በደስታ የሰነበተ ሰውነታቸው ወዲያው በጾም ሲደርቅ በሽታ እንዳያመጣባቸው ለጥንቃቄ ነው ይላሉ፡፡ የሳምንቱንም ስም "የአይብ ሳምንት ወይም ነጭ ጾም" ይሉታል፡፡
የመጨረሻው ሳምንት ሕማማት ነው፤ ሐዋርያት የጌታችን መከራ መስቀል እያሰቡ የጦሙት ነው ይላሉ፤ ያም ሆነ ይህ ሁሉም ከዐቢይ ጾም ጋር እንደ መርገፍና እንደ እጀታ ስለተያያዘ ከዐቢይ ጾም ይቈጠራል፡፡ ዐቢይ ጾም መባሉም የጌታ ጾም ስለሆነ፣ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኃጣውእ) ድል የተነሱበት፣ ድል የሚነሱበት ስለሆነ ነው፤ በሕዝቡም ዘንድ ሁዳዴ ይባላል፡፡ ሁዳድ ማለት የመንግሥት መሬት የመንግሥት ርስት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ሁዳድ በሚታረስበት ጊዜ፣ አዝመራው በሚሰበሰብበት ጊዜ ልጅ አዋቂ ሳይባል የመንግሥቱ ዜጋ ሁሉ ለሥራ ታጥቆ እንደሚነሣ፤ ይህንም የጌታን ጾም የጌታን ሁዳድ የክርስቶስ ዜጎች የሆኑ ምእመናን ሁሉ ይጾሙታል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶና አጠናቅሮ የተናገረው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በሁዳዴ ለሚገኙት እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ስለሠራላቸው እያንዳንዱ እሑድ በመዝሙሩ ስም ይጠራል፡፡

1. የመጀመሪያው እሑድ፡- ዘወረደ ይባላል፡፡ በመጽሐፉ መጀመሪያ አምላክ ከሰማይ መውረዱን፣ ሰው መሆኑንና መስቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡ ሙሴኒም ይሉታል፡፡ ምናልባት ስለሙሴ ሕግና ጾመ ሙሴን ስለሚያነሣ ይሆናል፡፡

2. የሁለተኛው እሑድ፡- ቅድስት ይባላል፡፡ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ይሆናል፡፡

3. የሦስተኛው እሑድ፡- ምኲራብ ይባላል፡፡ በዚህ ሰንበት ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ በምኲራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል፡፡

4. ዐራተኛው እሑድ፡- መፃጉዕ ነው፡፡ ድውያንን መፈወሱን፣ ዕውራንን ማብራቱን፣ የሚያነሣ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡

5. አምስተኛው እሑድ፡- ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሁኖ ያስተማረው የዳግም ምጽአትን ነገር የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡

6. ስድስተኛው እሑድ፡- ገብርኄር ይባላል፡፡ የጌታውን ብር ተቀብሎ ያተረፈበት፣ በጌታውም ፊት ምስጋናን ያገኘው ሰው ታሪክ ይዘመርበታል፡፡

7. ሰባተኛው እሑድ፡- ኒቆዲሞስ ነው፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር የነበረውን የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡

8. ስምንተኛው እሑድ፡- ሆሣዕና ነው፡፡ ጌታ በአሕያ ውርንጭላ ሆኖ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ ከሠርከ ሆሣዕና እስከ ትንሣኤ ያለው ሰባት ቀን ሕማማት ይባላል፡፡ በእነዚህ ቀኖች ውስጥ ብዙ አዝማደ መባልዕት አይበሉም፡፡ ስግደት ይሰገዳል፡፡ የጌታን መከራና ሞት የሚያስታውሱ ምንባባት፣ ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከድርሳናት ተወጣጥተው በግብረ ሕማማት ይነበባሉ፡፡ አዳም ከፈጣሪው ተጣልቶ የኖረውን የጨለማና የመከራ ዘመን በማስታወስ መንበረ ታቦቱ በጥቁር ልብስ ይሸፈናል፡፡ ልብሰ ተክህኖውም ጥቋቁር ነው፡፡
ሐሙስ፡- ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበትና ከእነርሱም ጋር ግብር ያገባበት ምሥጢረ ቊርባንን ያሳየበት ዕለት ነው፡፡ "ፈረንጆች" ዕለቱን "Monday፣ Thursday ወይም " the last supper" ይሉታል፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት የግብረ ሕማማቱ መጽሐፍ እንደሚያዘው ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ከቅዳሴው ቀደም ብሎ ቄሱ ውሀውን በብርት አድርጎ በጌታ አምሳል የምእመናንን እግር ያጥባል፡፡ ጸሎተ ቅዳሴው ከተፈጸመ በኋላ ምእመናኑ ወደየቤታቸው ሂደው ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዳቦና ጒልባን ይበላሉ፡፡ ለትንሣኤ የተዘጋጀውም ጠላ የሚቀመሰውም የዚያ ዕለት ነው፡፡ ስለ ሕፅበተ እግር ካነሣን ዘንድ በሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት የሚታጠቡት በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አምሳል አሥራ ሁለት ሰዎች ናቸው፡፡ በእኛ ግን በቤተ ክርስቲያናት ያሉ ሁሉ ሴትም ሆነ ወንድ ይታጠባሉ፡፡ ነገር ግን አሠራራችን ምሳሌ ስለሚያጥረው እኛም እንደነርሱ አሥራ ሁለት ሰዎችን ብናጥብ የሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡
ከጸሎተ ሐሙስ በበነጋው ዓርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ዕለት አጎበር ተሠርቶ ለስቅለቱ ነክ የሆኑ ምንባባት ሲነበቡ ይዋላል፡፡ ስግደቱም ከሰሞኑ ሁሉ የበለጠ ነው፡፡ ሠርክ ሲሆን እያንዳንዱ ምእመን ወደ ቄሱ እየቀረበ በሰሙነ ሕማማት ውስጥ የሠራውን ኀጢአት ይናዘዛል፡፡ ቄሱም በወይራ ቅጠል እየጠበጠበ ተጨማሪ ስግደት ይሰጣል፡፡ በአሥራ ሁለት ሰዓት ሠርሖተ ሕዝብ ይሆናል፡፡ ሁለት ቀን የሚያከፍሉ እህል ውሃ ሳይቀምሱ ያድራሉ፡፡ የማያከፍሉ ግን ከሐሙስ የተረፈውን ጉልባንና ዳቦ ይላክኩታል፡፡
"ቅዳሜ ጠዋት ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ› ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ፡፡ ሰላምን ፈጠረ፡፡ የምሥራች እየተባለ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበ ሁሉ ቄጠማ ይሰጣል፡፡ የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ምእመናኑም እየሰነጠቁ በራሳቸው ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡትም ካህናት በየበኩላቸው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው፣ ቄጠማውን የምሥራች እያሉ ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም ገንዘብ ያለው፣ ገንዘብ ይሰጣል፡፡ ገንዘብ የሌለው ደግሞ ለጧፍ የሚሆን "ማግ" ልቃቂት ይሰጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከማዕዶት እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉትን ዕለታት ተከፋፍለው ይዘው ለሰበካቸው ካህናት ምግብ እያዘጋጁ ያመጣሉ፡፡ በጐንደርና በላስታ ሁሉም በአንድ ላይ በደጀ ሰላም ይመገባሉ፡፡ ወይንም ምእመኑ ካህናቱን በቤቱ ይጋብዛል፡፡ በአዲስ አበባና በሸዋ ግን ወደየንስሐ አባታቸው ቤት ምግብ እያዘጋጁ ይወስዳሉ፡፡ የአክፋይ ይሉታል፡፡ በዚያ ግን ገብረ ሰላመ ነው የሚባለው፡፡ ይህች ቅዳሜ፡- "ሰንበት ዓባይ" ትባላለች የፊተኛዪቱ ቅዳሜ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ ከሥራው ያረፈባት ዕለት እንደሆነች፣ ይህች ደግሞ የሦስት ዓመት ከሦስት ወር የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ፈጽሞ በከርሠ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት ናት፡፡ ሁለተኛም ይህች ዕለት ‹ስዑር ቅዳሜ› ትባላለች፡፡ ስዑር መባሏም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ነው፡፡ በባላገር ግን ‹ስዑር› ያለውን ይዘው ሰሞኑን ምንም ሳይሠሩ ሰንብተው በዚህ ዕለት ይሠራሉ፡፡ "ቅዳሜ ሹር" እንዲሉ ቄጠማው የምሥራች ምልክት መሆኑ ከታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ዓለም በንፍር ውሃ በተጥለቀለቀ ጊዜ፣ የኖህ መርከብ ማረፊያ አጥታ ስትንሳፈፍ የውሃውን ሁኔታ ለመረዳት ኖህ ርግብን በመርከቡ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፡፡ እርስዋም ቄማጠ ባፏ ይዛለት ትመለሳለች፡፡ ኖህ በዚህ ቄጠማ የውሃውን መድረቅ ተረድቶ ተደሰተ፡፡ መርከቡንም ለማሳረፍ ተዘጋጀ፡፡ ቄጠማ ለጥፋት ውሃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ፣ አሁንም በክርስቶስ ሞት ማየ ሥራዌ፣ ማየ ድምሳሴ ኀጢአት፣ ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፣ የምሥራች ሲባባሉ ምእመናን ቄጠማ ይዘው፣ ቄጠማ አስረው ይታያሉ፡፡ በዚህች ዕለት በአንዳንድ ቦታ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ በአንዳንድ ቦታ አይቀደስም፡፡ የሚቀድሱት የሚሰጡት መልስ ካሣ የተፈጸመው ዓርብ ነው፡፡ ቅዳሴ መኖሩን የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጻፈው የዕለቱ "ክብር ይእቲ" ለማወቅ ይቻላል ይላሉ፡፡ አይቀደስም የሚሉት ደግሞ ምንም እንኳ የምንቀበለው ሥጋ፣ ነፍስ የተለየው፣ መለኮት የተዋሐደው ቢሆንም በትንሣኤ ድል ማድረጉን ከማየታችን በፊት መሥዋዕት አንሠዋም፡፡ ያሬድ የሠራው "ክብር ይእቲ" ቀድሱ የሚል ትእዛዝ የለውም ቅኔ ነው ይላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በቅዳም ስዑር ቅዳሴ እንዳይቀደስ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖአል፡፡

ክፍል አንድ.......በቅርቡ ክፍል ሦስት

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

3 comments:

  1. የአጽዋማት ሥርዐት
    ሊቀ ሥዩማን ራደ አስረስ
    ክፍል አንድ
    አጽዋማት፡- ጾም ለተወሰነ ሰዓት ከሁሉም ምግብ መከልከል ሁሉንም ምግብ መተው ነው፣ ለተወሰኑ ቀናት ማለት የጾሙ ቀናት እስኪያልፍ ድረስ ከተወሰኑ ምግቦች መከልከል የተወሰኑ ምግቦችን መተው ነው፣ ይኸውም ጥሉላትን ፈጽሞ መተው ሰውነትን ከመብልና ከመጠጥ መከልከል መጠበቅ ነው፡፡ ጾም ከጥሉላት መከልከል ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችን ከሚጐዳ ነገር ሁሉ መከልከልንና ለሌሎች መልካም ሥራ መሥራትንም ይጨምራል፡፡

    በማንኛውም የሃይማኖት ሥርዓት ጾም አለ፤ የአፈጻጸሙ ሥርዓት ግን የተለያየ ሁኖ ይታያል፤ ለምሳሌ ያህልም ዕብራውያን ሲጾሙ ውለው ማታ ጥሉላት ይመገባሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የክርስትናው እምነት ተከታይ እንደእኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ሲጾሙ ውለው ሰዓት ሲደርስ እህልና ውሃ ብቻ ይቀምሳሉ እንጂ የጾሙ ወር ወይም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ጥሉላት ፈጽሞ ክልክል ነው፤ የአጽዋማት ሥርዓት ሲባል ጾም እንዴት እንደሚገባና እንዴት እንደሚወጣ፣ እንዴትና ለምን እንደሚጾም ለይቶ ማወቅና እንደ ሥርዓቱ መፈጸምን የሚያመለክት ነው፤ የጾምን አላማና ጥቅም በሚመለከት የሸዋ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ "የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" በሚለው መጽሐፋቸው "የበዓላትና የአጽዋማት ቀኖና" በሚል ርእስ እንደሚከተለው ገልጠውታል፡፡ "ጾም /ጦም/ ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል መወሰን ማለት ነው፡፡ ወይም ለሰውነት የሚያምረውንና የሚያስጐመዥውን ነገር መተው ማለት ነው፡፡ ጾም ከሃይማኖት ጋር ዘለዓለማዊ ዝምድና ስላለው ሃይማኖት ባለበት ቦታ ሁሉ ጾም አለ፡፡ ይልቁንም በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህልና ውሃ በአፋቸው አይገባም ነበር፡፡ /ዘፀ፡34፡28/ በኀጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር፡፡ /ዮናስ 2፣7-10/ "በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ራሱ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥራ መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡(ማቴ 4፣2፤ ሉቃ.4፣2) ይህም ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት አብሮ የሚኖር መንፈስ ርኩስ ሰይጣን እንኳ በጾም የሚወገድ መሆኑን መድኀኒታችን ተናግሮአል፡፡ (ማቴ.17፣21፤ ማር.9፣2) ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም በየጊዜው ከመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾምና በጸሎት ላይ እንዳሉ ነበር፡፡ (የሐ.ሥራ 13፣2) ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስትም የሚሾሙት በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ (የሐ.ሥራ 13፣3፤ 4፣23፤) እነቆርኔሌዎስ ያላሰቡትን ያዩና ያገኙ በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ማልደው ነው፡፡ (የሐ.ሥራ 10፣30) "የጾም ሃይማኖታዊ ትርጒም ፈጣሪን መለመኛ ከኀጢአት ቊራኛ መላቀቂያ መሣሪያ ስለሆነ በጾም ወራት ላምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኀይል ተቃራኒ የሆነ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ የአልኮል መጠጦችን፣ ሥጋንና ቅቤን፣ ወተትንና እንቁላልን ማራቅ ታዟል፡፡ ከመባልዕትና ከሌላው ደስታ ሁሉ ጋር ባልና ሚስት በምንጣፍ በአልጋ አይገናኙም፡፡ (1ቆሮ.7፣5) ጾም በትምህርተ ሐዋርያትና በሊቃውንትም ዘንድ ሲሰበክ ኑሯል፡፡ ነዳያንን ለመመገብ የሚጾም ንዑድ ነው፤ ክቡር ነው፡፡ እንደተባለ ጦመኛው ለምሳው ወይም ለራቱ ያለውን ወጭ ነዳያን እንዲረዱበት ለድኩማን መርጃ ድርጅት ወይም በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ነዳያን መስጠት ጾሙን የበለጠ ክርስቲያናዊ ያደርገዋል፡፡ "ጾም የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ ከኀጢአት ለመንጻት ስለራሱ የታሰበውን ለነዳያን በመስጠት የሚጾም መሆኑን ተረድተናል፡፡ ጾም ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም፤ ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለጠላትም ይጾማል፤ ‹ለሚያሳድዱህ ጹምላቸው› እንደተባለ (ዲድ፡1፣3፤) በደዌ ዳኛ በአልጋ ቊራኛ የተያዙትን፣ በምርኮና በስደት ያሉትንም በጾም ወራት ማስታወስና መጸለይ ይገባል፡፡ በጾም ወራት ከመባልዕት መከልከል ብቻ ሳይሆን ዐይን ክፉ ከማየት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፣ ጆሮ ክፉ ከመስማት መቆጠብ እንደሚገባ ተጽፎአል፡፡ "ይጹም ዐይን፣ ይጹም ልሳን፣ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ኀሡም በተፋቅሮ" (ቅዱስ ያሬድ ድጓ) በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ባህልና ትውፊት ውስጥ ያሉ የምዕራብም ሆኑ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ከሐዋርያት የወረሱት የጾም ሕግና ሥርዐት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ከመጀመሪያዎቹ አብያተ ክርስቲያናት አንድዋ ስለሆነች ይህ የጾም ሕግና ሥርዓት አላት፡፡ በሕጓም መሠረት ሰባት የጾም ወራት አሏት፡፡ እነርሱም፡-

    1. ዐቢይ ጾም፣

    2. ጾመ ሐዋርያት፣

    3. ጾመ ፍልሰታ፣

    4. ጾመ ሐዋርያት፣

    5. ጾመ ገሃድ፣

    6. ጾመ ነነዌ፣

    7. ጾመ ድህነት ናቸው፡፡

    ReplyDelete
    Replies
    1. 1. ዐቢይ ጾም፣

      2. ጾመ ሐዋርያት፣

      3. ጾመ ፍልሰታ፣

      4. ጾመ ነቢያት፣

      5. ጾመ ገሃድ፣

      6. ጾመ ነነዌ፣

      7. ጾመ ድህነት ናቸው፡፡

      Delete
  2. God help Ethiopian ortodox

    ReplyDelete